ሴቶች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ፣ በማህበራዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብት አላቸው!!! የሶማሌ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በክልሉ ዋና ከተማ ጅጅጋ በየዓመቱ በሚካሄደው በዘንድሮው የእግር ኳስ ውድድር ላይ ሴት ታዳሚዎች እንዳይታደሙ ከልክሏል፡፡ ለዚህም ያቀረበው ምክንያት “ሴቶች ከስፖርታዊ ጨዋነት ወጣ ያለና የጨዋታውን ህግ የማያከብር ተግባር ይፈፅማሉ” የሚል ምክንያት ነው፡፡
ይህ ውድድር ደግሞ ከስፖርታዊ ውድድር በዘለለ የክልሉ ህዝብና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሚጠቀሙበት እንዲሁም ድጋፋቸውን የተለያዩ ድምጾችን በማሰማትና በሙዚቃ መሳሪያ እያደመቁ በመግለጽ የሚሳተፉበት ውድድር መሆኑ ተገልጿል፡፡ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት እንዳለው ይታወቃል፤ ሆኖም ግን በተወሰኑ ሰዎች ስህተት ወይም ጥፋት ሁሉንም የክልሉ ሴቶች ከስፖርታዊ ጨዋነት ተግባር ውጪ እንደሆኑ በመፈረጅ በውድድሩ መሳተፍና መታደም እንዳይችሉ ማገድ በአጠቃላይ የክልሉን ሴቶች ሰብዓዊ ክብር እንዲሁም መልካም ስም የሚያጎድፍና በልዩነት የሴቶችን ክብር የሚነካ ድርጊት በመሆኑ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከዚህ ድርጊቱ ሊታረምና ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል፡፡
በተጨማሪም ማንኛውም ሰው ሃሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዳለው በህገ መንግስታችን ተደንግጓል፤ይህ መብት ሊገደብ የሚችልበት አግባብ ግን የሰዎችን ሰብዓዊ ክብርና መልካም ስም የሚያጎድፍ ሲሆንና ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ሲባል ሊገደብ ይችላል፣ በተጨማሪም በመብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ህጋዊ ገደቦችን ጥሶ ሲገኝ በህግ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡
ይህ ሲሆን ግን ጥፋቱን ፈፅሞ የተገኘ አካል ወይም ግለሰብ ላይ በህገ መንግስቱ እንዲሁም በስነ-ስርዓት ህጉ መሰረት በሚመለከተው አካል ምርመራ ተደርጎበት በግለሰቡ ላይ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል እንጂ በሴቶች ላይ በጅምላ የተወሰደው እርምጃ ሴቶች ባህላቸውን እንዳያንጸባርቁ፣ በማህበራዊ መስተጋብሮቻቸው ላይ በነፃነት እንዳይሳተፉ፣ ሃሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ የሚያደርግና የሴቶችን እና የወንዶች የእኩልነት መብት የጣሰ እርምጃ ከመሆኑም በላይ ሌሎች ሴቶች መብታቸውን እንዳይጠቀሙና እንዳይተገብሩ ተስፋ የሚያስቆርጥ ድምዳሜ የተሰጠው ውሳኔ ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ይህ ድርጊት በአስቸኳይ እርምት እንዲደረግበት፣ ውሳኔውን የሰጠው ቢሮ እና ግለሰብም በሃላፊነት እንዲጠየቁበት እና የክልሉ ሴቶችም በይፋ ይቅርታ እንዲጠየቁ ያሳስባል፡፡
#የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር
#የፆታ እኩልነትን ያላገናዘበ አግላይ ውሳኔ ይቁም!
#ሴቶች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ የመሳተፍና የመደገፍ መብት አላቸው!
#ሴቶችን ከማህበራዊና ባህላዊ መስተጋብር መገደብና ማግለል ይቁም!
#ሴቶች ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ መብት አላቸው!
1
21317:03
